የዶር ደሳለኝ መልዕክት
በግራም ይሁን በቀኝ የሞቱት የአማራ ውድ ልጆች መሆናቸው እየታወቀ አንዱን አጥፊ ሌላውን ጠፊ አድርጎ በመፈረጅ የሕዝቡን አንድነት ለማዳከም የሚደረገው የቃላት ዘመቻ ትርጉም አልባ ድካም መሆኑን ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ተናገሩ።
****
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፕሬዚዳንት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ከአብመድ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሰኔ 15/2011 ዓ.ም በተፈፀመው ጥቃት ንቅናቄው ከፍተኛ ሐዘን እንደተሰማው ገልፀዋል፡፡ አብን መላው የአማራ ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ይህን የፈተና ጊዜ በማለፍ አንድነቱን እንዲያጠናክር እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ክስተቱ በተፈጠረበት ወቅት የንቅናቄው አባላት ሐዘንተኞችን እንዳፅናኑም አስታውሰዋል፡፡ አብን ሁሉም የአማራ ሕዝብ አንድነቱን በማጠናከር ያጋጠመውን የፈተና ጊዜ ማለፍ እንደሚገባ እየሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሕዝቡ አሁን ከተፈጠረው አደጋ ወጥቶ ወደ ተሻለ ሠላም እና መረጋጋት እንዲያመራ ሕዝባዊ ውይይቶችን ለማድረግ አብን በዝግጅት ላይ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ ሕዝቡ ያጋጠመውን ጉዳይ በመቋቋም የቆየ ማኅበራዊ ጥብቅ ቁርኝቱን ተጠቅሞ አንድነቱን እንዲያጠናክር ፓርቲው በተለያዩ አጋጣሚዎች መልዕክቶችን እያስተላለፈ እንደሚገኝም የንቅናቄው ፕሬዝዳንት ተናግረዋል፡፡
በተፈጠረው ችግር በደረሰው የሰው ሕይወት ማለፍ የገዥው ፓርቲ አዴፓ መዋቅር ውስጥ የአመራር ክፍተት በመፈጠሩ፣ አዴፓ ሕዝቡን በማይጎዳ መልኩ ክፍተቱን አርሞ ወደፊት እንዲራመድ የሚስፈልገውን የሞራል ድጋፍ አብን እየሰጠ እንደሚገኝ ዶክተር ደሳለኝ ገልጸዋል፡፡
ዶክተር ደሳለኝ ከምንም በላይ ይህ ወቅት አብንን ጨምሮ በክልሉ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለክልሉ ሕዝብ ሕልውና ዘብ የሚቆሙበት በመሆኑ የእርስ በእርስ ሽኩቻዎችን ወደ ጎን መተው እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡ እርሳቸው የሚመሩት ንቅናቄ ከአዴፓም ይሁን ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተባብሮ ለመሥራት እና የሕዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡
የሕዝቡ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም ከአዴፓ ጋር ጅምር ሥራዎችን በጋራ ሲያከናውን የነበር መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ደሳለኝ በቀጣይም ግንኙነቱን ለማጠናከር እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡
በአደጋው ዘመድ ወዳጆቻቸውን ያጡ ቤተሰቦች የሚፅናኑበት እና ሊደገፉ የሚገባበት ወቅት በመሆኑ መላ የክልሉ ሕዝብ ከጎናቸው በመቆም ወገናዊ አለኝታውን ሊያሳያቸው እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በግራም ይሁን በቀኝ የሞቱት የአማራ ውድ ልጆች መሆናቸው እየታወቀ አንዱን አጥፊ ሌላውን ጠፊ አድርጎ በመፈረጅ የሕዝቡን አንድነት ለማዳከም የሚደረገው የቃላት ዘመቻ ትርጉም አልባ ድካም መሆኑ ሊታወቅ እንደሚገባም ዶክተር ደሳለኝ አስረድተዋል፡፡