የሕዝብን ስብጥር ሆን ብሎ ለመቀየር መስራት በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ሳይቀር የዘር ማጥፋት እንደሆነ ስንት ሰው ያውቃል?
በነ ዐቢይና ለማ ቴያትር አዳሜ ተደምረናል እያለ ሲደናበር የበላውና የጠገበው ሄዶ የራበውና ሁሉ ብርቁ መተካቱን፤ የቆላን ተወግዶ የሚያሳርረን መምጣቱን የታየንን ብንናገር ሁሉ እብደት ላይ ስለነበር የሚሰማ አልነበረም። እነሆ ዛሬ የለውጥ ሐዋርያዎቹ ለውጥ ማለት እኛን ማጥፋት ማለት እንደሆነ በአንደበታቸው ተገለጡ። ተንታኝ ዶክተርና ፕሮፌሰሮች ሳይቀር አርቲስት ሺመልስ «እኛ ቲያትረኞችም በቲያትረኞች ተበልጠናል» ያለውን ያህል ማስተዋል የላቸው። ከጋዜጠኛ እስከ ምሁር፤ በተቃዋሚ እስከ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሁሉም እኛን ለማጥፋት በታቀደም ሴራ ተደምረው ቄስ ሞገሴዎች ሆነዋል።
እነሆ ዛሬ የለውጡ መሪና ሐዋርያ ተደርጎ በኛዎቹ ቄስ ሞገሴዎች ሳይቀር ሲደሰኮርለት የከረመው «ኢትዮጵያ ሱሴው» ሀሳዊው መሲህ ለማ መገርሳ እንኳን ሊለውጠን ሊያጠፋን እየሰራ መሆኑን በአንደበቱ የተናገረው ርዕዮት ሬዲዮ ምስጋና ይግባው ተርጉሞ አስደምጦናል። ለማ ሊያጠፋን እየሰራ መሆኑን የተናገረው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ከዐቢይ አሕመድ ጎን ተቀምጦ ነው። ዐቢይም ለማ የአዲስ አበባ ሕዝብ ስብጥር ለመቀየር እየሰራ መሆኑን በተናገረው ላይ የምጨምረው የለኝም እሱ ጨርሶታል ብሎ ተጋርቶት አልፏል።
በዚህ ነውረኛ ቢባል ሊገልጸው በማይችለው አይን የወንጀል ተግባር ለማ መገርሳ የአዲስ አበባን ሕዝብ ስብጥር ወይንም demography ለመቀየር አቅዶ እየሰራ መሆኑን፣ ለዚህም ተግባራዊነት 500,000 ኦሮሞዎችን ወደ ተፈናቀሉበት ወደ ሶማሌ ክልል መመለስ ሲችል አልያም ወደ ቅያቸው ወደ ሐረር ማስፈር እየተቻለ በአዲስ አበባና በዙሪያው ያሰፈሯቸው የአዲስ አበባን የሕዝብ ስብጥር ኦሮሞን በሚያበዛ መልኩ ለመቀየር በማሰብ እንደሆነ ፤ ከዚህ በተጨማሪ 500,000 የሚሆኑ ኦሮሞ የመንግሥት ሰራተኞችንም የከተማን የሕዝብ ስብጥር ለመቀየር ሲባል በከተሞች ማስፈሩን በአንደበቱ አረጋግጦልናል። እነ ቄስ ሞገሴ አሁንስ ምን ይሉ ይሆን?
ለማ መገርሳና ዐቢይ አሕመድ የአዲስ አበባን ሕዝብ ስብጥር ለመቀየር እየሰሩ መሆኑን በአንደበታቸው የተናገሩት ፕሮጀክታቸው ኦሮምኛ ለማይሰማው ሕዝብ መገለጡ በተለይ ለውጥ መጣ ብለው የዳኝነትና የፍትሕ ስርዓቱን የተቀላቀሉ እንደ መዓዛ አሸናፊ አይነት ሰዎች ለፍትሕ ያላቸው ቀናኢነት አልያም እንደከዚህ በፊቶቹ አገዛዝ አገልጋይ መሆን አለመሆናቸው የሚፈተሽበት testing moment ይመስለኛል።
የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 269 የሕዝብን ስብጥር ወይንም demographyን ለመቀየር መስራት የዘር ማጥፋት እንደሆነ ይደነግጋል። ይህ ማለት የአዲስ አበባን ሕዝብ ስብጥር ለመቀየር በእቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን የነገረንን ለማ መገርሳን በዘር ማጥፋት መከሰስ አለበት ማለት ነው። የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያዎች የዘር ማጥፋት እያካሄደ ያለውን ለማ መገርሳንና ተባባሪውን ዐቢይ አሕመድን በዘር ማጥፋት ወንጀል ፍርድ ቤት ማቆም ባይችሉ ክስ መስርተው ታሪክ ይሰሩ ይሆን?
አርቲስት ሺመልስ አበራ «ላለፉት 27 ዓመታት አፋችንን ሸብበን በመቀመጣችን በሀገራችን ብዙ ግፍና መከራ እንዲያልፍ ምክንያት ሆኗል፡፡ አሁን ግን ይህን አምባገነናዊ የሚመስል አካሄድ በአጭሩ ልናስቆመው ይገባል።ለውጡን ሁሉም በጥርጣሬ ልናየው» ሲል የተናገረው ማስተዋል የሚጣላ ሕሊና ይፈጥርባቸው ይሆን? የሚታይ ይሆናል!
እኛ ግን እንደትናንትናው ሁሉ ዛሬም እንዲህ እንላለን…
{[ዳ] ጠብቆ ይነበብ}
ሙሴ መጣ ብለህ መለከት ስትነፋ፣
የመጣልህ አ[ዳ]ኝ ከፈርኦን ከፋ።