Breaking News
Home / Amharic / ዜግነትን መቀየር ማለት ምን ማለት ነው ? Important ! Look Jawar’s new ID Card !

ዜግነትን መቀየር ማለት ምን ማለት ነው ? Important ! Look Jawar’s new ID Card !

ዜግነትን መቀየር በተመለከተ አንዳንድ ነጥቦች


ባይሳ ዋቅ-ወያ (ቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣን የነበሩ የዓለም አቀፍ ሕግ ባላሙያ)

ከጥቂት ወራት በፊት ስለ አንዳንድ የውጭ አገር ዜግነት ከነበራቸውና በዶ/ር ዓቢይ ጥሪ መሠረት ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ የኢትዮጵያ ዜጋ ባለመሆናቸው ያጋጠማቸውን አስመልክቼ አንድ ጽሁፍ በተለያዩ ሚዲያዎች አሳትሜ ነበር፡፡ ዛሬም ጥያቄው ወቅታዊ የሆነና ከሕግ አንጻር ትንታኔና ገለጻ እንደሚያስፈልገው ስለተረዳሁ በፊተኛው ጽሁፌ ላይ ተመርኩዤ ይህንን ጽሁፍ ለማቅረብ ወሰንኩ፡፡ ዓላማዬም ዜግነትን የመሰለ ለማንኛውም ሰብዓዊ መብት ቁልፍ የሆነውን ጉዳይ በቀላሉ እንዳናይና ይህንን በሕይወታችን ወሳኝ የሆነውን “ዜግነትን የመቀየር” እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት ከሕግ አንጻር ማድረግ ያለብንና መከተል ያለብንን ሂደት ችግሩ ላጋጠማቸውና ለወደፊትም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ ለሚፈልጉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አስፈላጊውን ሕጋዊ ምክር ለመስጠት ነው፡፡

ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱ “ኢትዮጵያውያንን” በሁለት ቦታ ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ አብዛኞቹ በገዛ ፈቃዳቸው የውጭ አገር ዜጋ የሆኑ ሲሆን፣ በጣም ጥቂቶቹ ደግሞ፣ ዜግነታቸውን ሳይቀይሩ በመኖርያ ፈቃዳቸው (ለምሳሌ ግሪን ካርድ) ብቻ ለዓመታት የኖሩ ናቸው፡፡ በውጭ አገር ይኖሩ በነበረበት ዘመን የኢትዮጵያዊነት ዜግነታቸውን ይዘው የቆዩት ግለሰቦች ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ከቢሮኪራሲውና የኑሮ ዘይቤ ጋር መላመድ ያቅታቸው እንደሆን እንጂ እንደ ኢትዮጵያ ዜጋ ባገራቸው ለመኖርም ሆነ በፈለጉት መልክ ተደራጅተው ወይም ከተደራጁት ተቀላቅለው ባገሪቷ የፖሊቲካ ሂደት ለመካፈል ብሎም ለመምረጥና ለመመረጥ የሚያጋጥማቸው ችግር አይኖርም። ችግሩ ያለው፣ የውጭ አገር ዜግነትን በወሰዱ ግለሰቦች ዘንድ ነው። እንደሚገባኝ ከሆነ፣ ሁላችንም በትውልድ ኢትዮጵያዊ ስለሆንን ብቻ፣ በተለያዩ ምክንያቶች የሌላ አገር ዜግነት እንኳ ከወሰድን በኋላ፣ የኢትዮጵያዊ ዜግነታችን ለዘላለም ጥያቄ ውስጥ የማይገባና ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሆነን እንደተወለድን ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሆነን የመሞት መብት ያለን ይመስለናል። ይህን ከሕግ አንጻር ስናየው የተሳሳተ አመለካከት ነው። መነሾውም ምናልባት ዜግነት የሚባለውን እሳቤ እንደ ሰብዓዊ መብት ከመቁጠር የተነሳ ይመስለኛል። ዜግነትን የመስጠትም ሆነ የመንሳት መብት ያለው መንግሥት ስለሆነ ዜግነት የሰብዓዊ ሳይሆን የሕጋዊ መብት እንደሆነ ማወቁ ተገቢ ይመስለኛል።

ዜግነትን መቀየር፣ በተለይም ለረጅም ዘመን ከኖሩበትና ከሠሩበት፣ ቤተሰብ ካፈሩበትና ልጆችን ካሳደጉበት አገር ትቶ የሌላ አገር ዜጋ (የትውልድ አገር ዜግነትም ቢሆን) ለመሆን መወሰን ያማያስመኝ እርምጃ ነው፡፡ በተለይም እንደ አሜሪካ ካሉ ያደጉ አገራት ለዓመታት የሠሩበትንና ያከማቹትን የልፋት ዋጋ ጥሎ የሌላ አገር ዜጋ ሆኖ አዲስ ሕይወት ለመጀመር መወሰን በጣም ከባድ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም አንዴ የአሜሪካ ዜግነትን አልፈልግም ብሎ ከተወጣ መመለሻ የለምና!

ወደ ዋናው የዜግነት መቀየር ጉዳይ ከመምጣታችን በፊት ከጉዳዩ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸውን አንዳንድ እውኔታዎችን ባጭሩ መዳሰስ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡

ሀ) ዜግነት በሰው ልጅ ምድራዊ ሕይወት ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ የያዘ ሕጋዊ መብት ነው፡፡ “ዜግነት አልባ” ሰው ዜግነት ካላቸው ሰዎች እኩል የሕጋዊ መብቶች ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህም ነው የዜግነት አልባ መሆንን ችግር በመረዳት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ1961 ዓ/ም “ዜግነት አልባነትን ለመቀነስ” የሚል ዛሬ ወደ ሰባ የሚጠጉ አገራት ያጸደቁትን ኮንቬንሽን ያወጀው፡፡ የዚህ ኮንቬንሺን ዋናው ዓላማ ግለሰቦች ያለዜግነት እንዳይቀሩ መንግሥታት የተቻላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት አንድ ዜጋ፣ ዜግነቱን ለመቀየር አግባብ ላለው የመንግሥት መሥርያ ቤት ሲያመለከት፣ ጥያቄውን የሚያስተንግደው መንግሥት ዜጋውን ከማሰናበቱ በፊት፣ “ዜግነት አልባ” እንዳይሆን ብርቱ ጥንቃቄ ያደርጋል፡፡

ለ) ዜግነት ሕጋዊ እንጂ ሰብዓዊ መብት አይደለም፡፡ ያገሩ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ዜጎችን የመምረጥ ወይም የማሰናበት መብት ያለው መንግሥት ብቻ ነው፡፡ ግለሰቦች በተለያዩ ምክንያቶች በትውልድ ያገኙትን ዜግነታቸውን ትተው በገዛ ፈቃዳቸውና ያላንዳች ጫና የሌላ አገር ዜጋ መሆን ይችላሉ፡፡ መንግሥታት ግን ግለሰብን ያለፈቃዱ(ዷ) አስገድደው ዜጋ ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ነው ዛሬ በመላው ዓለም የምንገኘው ትውልደ ኢትዮጵያውያን አገራችንን ስንለቅ ተገድደን ቢሆንም የውጭ አገር ዜግነትን የተጎናጽፍነው ግን በፍላጎታችን ብቻ ነው፡፡ ጥገኝነት በጠየቅንባቸው አገራት ሳይቀር፣ ዜግነታችንን ሳንቀይር “በመኖርያ ፈቃድ ዶኩሜንት” ብቻ መኖርና ካገር አገር መንቀሳቀስ እንችል ነበር፡፡ የጥገኝነት አገሮቻችንን ዜግነት የወሰድነው በበጎ ፈቃዳችን ካገሬው ዜጎች እኩል መብት ለመጎናጸፍ ተብሎ እንጂ ተገድደን አይደለም ማለት ነው፡፡

ሐ) ዜግነትን መቀየር የግለሰብ ሕጋዊ መብት ቢሆንም አንድ ሰው ዜግነቱን እንዳሻው ሊቀይር አይችልም፡፡ ሕጉን ተከትሎ መሆን አለበት፡፡ ሕጎቹም እንደያገሩ ቢለያዩም አንድ የሚጋሩት ነገር ቢኖር፣ ሁላቸውም ዜግነትን የመቀየር ሕጋዊ መብት አለመገደባቸው ነው፡፡ ለዚህም በየሕጋቸው ውስጥ ያካተቱትና መሟላት ያለባቸው ግዴታዎች አሉ፡፡

መ) ብዙዎች ሰዎች ፓስፖርትን እንደ ዜግነት መታወቂያ ዶኩሜንት አድርገው ይገምታሉ፡፡ ይህ በከፊል ስህተት ነው፡፡ ፓስፖርት የዜግነት ማረጋገጫ ሆኖ የሚያገለግለው የፓስፖርቱ ባለቤት ካገር ውጭ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ አንድ ግለሰብ ባገሪቷ ግዛት ውስጥ እስካለ ድረስ የዜግነት ማረጋገጫ ዶኩሜንቶቹ የኗሪነት መታወቂያ ወይም የመንጃ ፈቃድን የመሳሰሉ ናቸው፡፡ ዛሬ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ዜጎች ናቸው የምንላቸው ከመቶ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሲኖሩ ፓስፖርት ያላቸው ግለሰቦች ሚሊዮን አይሞሉም፡፡ አብዛኛው ሕዝባችን እንደ ዜግነት ማረጋገጫ የሚጠቀመው የቀበሌ መታወቂያ ወረቀትን ነው፡፡

ወደ ዋናው ጉዳይ ልመልሳችሁና፣

አብዛኛው ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሚኖረው በአሜሪካ አገር ስለሆነ ዋናው ትኩረቴ በዚህ አገር የዜግነት ሕግና ዜግነትን ለመቀየር አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ይሆናል፡፡ እንደ ዳሰስኳቸው ከሆነ የሌሎች አገራት የዜግነት ሕጎችም ጥቃቂን የሂደት ልዩነት ይኖራቸው እንደው እንጂ ከሞላ ጎደል ከዚሁ ከአሜሪካው ሕግ ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡

የአሜሪካ የዜግነት ሕግ፣ የግለሰቦችን የዜግነት መቀየር ሕጋዊ መብት ያከብራል፡፡ በያመቱ እስከ አምስት ሺህ የሚሆኑ የአሜሪካን ዜጎች ዜግነታቸውን የሚቀይሩ ሲሆን አብዛኞቻቸው ላገሪቷ መንግሥት የገቢ ግብር ላለመክፈል ሲባል ወደ ሌላ አገር የሚኮበልሉ ናቸው፡፡ ዜግነታቸውን ለመቀየር ለሚፈልጉ የአሜሪካ ዜጎችም ግልጽ የሆኑና አመልካቾቹ ማድረግ ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎችን ከሞላ ጎደል እንደሚከተለው አስቀምጧል፡፡

አመልካቹ በውጭ አገር ካሉት የአሜሪካ ኤምባሲ ቆንሲላዎች (ቢቻል ለወደፊት ሊኖርበት ባሰበው አገር የሚገኝ) መርጦ ዜግነቱን ለመቀየር መፈለጉን የሚያሳይ ማመልከቻ ማስገባት አለበት፡፡ ቆንሲላዎች እንደያገሩ የተለያዩ የማስፈጸሚያ ጊዜ ገደብ ስላላቸው፣ የትኛው ቆንሲላ ፈጥኖ ጉዳዩን እንደሚፈጽም ማወቅ የአመልካቹ ፈንታ ነው፡፡ ማንኛውም አመልካች ወደ ቆንሲላው ሄዶ ለኢንተርቪው ቀጠሮ ከመውሰዱ በፊት ግን ማመልከቻውን ለማስገባት ሲሄድ ይዞ መቅረብ ካለባቸው ሕጋዊ ዶኩሜንቶች ከአሜሪካው በተጨማሪ ሌላ ዜግነት እንዳለው የሚያሳይ የሌላ አገር ፓስፖርት በእጁ መያዝ አለበት፡፡ የነዚህን ሁለት ፓስፖርቶች ቅጂም ከማመልከቻው ቅጽ ጋር አያይዞ በአካል ቀርቦ ማስገባትና ለኢንተርቪው ቀጠሮ መውሰድ ግዴታ ነው፡፡ በተለምዶ፣ አመልካቹ ሁለት ፓስፖርት ስላለውና እስከሚቀጥለው ኢንተርቪው ድረስ የመንቀሳቀስ ችግር ስለማያጋጥመውና ከሁሉም በላይ “ለዜግነት አልባነት” ስለማይዳረግ፣ ቆንሲሉ በመጀመርያው ቀን ከሌሎች ዶኩሜንቶች ጋር የአሜሪካውንም ፓስፖርት ከአመልካቹ ይረከባል፡፡
አመልካቹ በባለሥልጣኑ (የአሜሪካ መንግሥት) የተዘጋጁትን ለተለያዩ ዓላማ የታቀዱትን ቅጽ DS-4079, 4080, 4081, 4082 እና 4083 የተባሉትን በትክክል መሙላትና ማመልከቻውን ፕሮሴስ ለማድረግ የሚረዳ $2,500 የአሜሪካን ዶላር በጥሬ ወይም በቼክ ፈርሞ መስጠት ይኖርበታል፡፡
መሞላት ካለባቸው ብዙ ቅጾች አንዱ፣ አመልካቹ ባለፉት አምስት ዓመታት እንደ አንድ የአሜሪካ ዜጋ በአሜሪካም ሆነ በውጭ አገር በኖረበት ወቅት አስፈላጊውን የመንግሥት ግብርና ቀረጥ በአግባቡ መክፈሉን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ኮፒ ይዞ መቅረብ አለበት፡፡
አመልካቹ በቆንሲላው የሚፈለጉ ዶኩሜንቶች በሙሉ መሟላታቸውን ካረጋገጠ በኋላ ለወደፊት ሊኖርበት በሚፈልግበት “አዲስ አገር” በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ቆንሲላ ጽህፈት ቤት ሄዶ ዶኩሜንቶቹን ለማስረከብ ቀጠሮ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ በቀጠሮው ቀን አመልካቹ በግንባር የመቅረብ ግዴታ አለበት፡፡
አመልካቹ የአሜሪካን አገር የቀረጥ/ግብር ዓመታዊ ፎርም (IRS 8854) መሙላቱን እርግጠኛ መሆን አለበት፡፡ ከአሜሪካ ዜግነት መላቀቅ ማለት ከግብር ዕዳ ነጻ መሆን ማለት ስላልሆነ በዚሁ በመጀመርያው ቀጠሮ ወቅት ይህንን ፎርም በትክክል ሞልቶ በቆንሲሉ ፊት ፈርሞ ማስረከብ አለበት፡፡ በሕጉ መሠረት የአመልካቹ ግለሰብ ዓመታዊ ገቢ ከአንድ መቶ ስድሳ አምስት ሺህ ዶላር በታች ከሆነ ግለሰቡ ዜግነቱን በመቀየሩ የሚያስከትለው ችግር እምብዛም አይኖርም፡፡ ከዚያ በላይ ጥሬ ሃብትና የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረት ያላቸው አመልካቾች ግን ለየት ያለ ፎርም መሙላት አለባቸው፡፡
ቆንሲሉም የቀረበለትን ዶኩሜንት ትክክለኛ መሆናቸውን ካረጋገጠ በኋላ በሚሠጠው ሁለተኛ ቀነ ቀጠሮ በግንባር ቀርቦ ቃለ መጠይቅ ማድረግ የአመልካቹ ግዴታ ነው፡፡ ከዚህ የመጀመርያው ቃለ መጠይቅና አመልካቹ ከሚፈጽመው መሃላ በኋላ ቆንሲሉ፣ ዜጋው “ዜግነትን ለመቀየር” ማመልከቻ ማስገባቱን ብቻ የሚያስረዳ ሴርቲፊኬት ለአመልካቹ ይሠጣል፡፡ የግለሰቡ የዜግነት መልቀቂያ ማመልከቻ በተለያዩ የአሜሪካ መንግሥት ተቋማት (CIA, FBI, Homeland Security, etc) በሚገባ ተጠንቶና አመልካቹ ዜግነቱን መልቀቁ የአሜሪካንን መንግሥት ጥቅም የማይነካ መሆኑ ከታመነበት በኋላ ወሳኙ የዜግነት መቀየር ሴርቲፊኬት (Certificate of Loss of Nationality – CLN) በአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒቴር ተፈርሞ በቆንሲሉ በኩል ለአመልካቹ እንዲደርስ ይደረጋል፡፡ የዜግነት መቀየር ሴርቲፊኬት ተፈርሞ እስኪመጣ ድረስ የተወሰነ የጊዜ ገደብ ባይኖረውም፣ በአማካይ ግን ከአምስት እስከ አሥራ አምስት ወራት እንደሚፈጅ ልምዶች ያመለክታሉ፡፡ በአሜሪካን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የተፈረመው “የዜግነት መቀየርያ ሴርቲፊኬት” (Certificate of Loss of Nationality – CLN) የመጨረሻውና ወሳኙ ከአሜሪካን ዜግነት የመላቀቂያ ማረጋገጫ ዶኩሜንት ነው፡፡

በሕግ መነጽር ካየነው ይህ ከአሜሪካን ዜግነት ለመላቀቅ የሚወሰደው እርምጃ፣ በዋናነት ሊተገበር የሚችለው አስቀድሞ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት አመልካቾቹ የአሜሪካ ዜጋ ሆነው እያለ ሌላ ተጨማሪ ዜግነት ባላቸው ግለሰቦች ላይ ብቻ ነው፡፡ በሕግ ቋንቋ፣ ጣምራ ዜግነት (dual nationality) ያላቸው ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ የዜግነት ሕግ ደግሞ ጣምራ ዜግነትን ስለማይፈቅድ ይህ የ “ሁለተኛ ፓስፖርት” ጉዳይ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከአሜሪካን ዜግነት ለመላቀቅ ሲፈልጉ ዋናው መሰናክል እንደሚሆንባቸው እሙን ነው፡፡ ታዲያ ከአሜሪካን ዜግነት ተላቅቆ የኢትዮጵያን ዜግነት መልሶ ለመወሰድ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምን ማድረግ አለባቸው? እስቲ ለማንኛውም የኢትዮጵያን የዜግነት ሕግ እንዳስስና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተመልሰው የኢትዮጵያ ዜጋ ለመሆን ሲፈልጉ ማሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች እንመልከት፡፡

የኢትዮጵያ የዜግነት ሕግ በአንቀጽ 20(1) ላይ፣ “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በራሱ ፍላጎት የሌላ አገር ዜግነት ካገኘ (ኢትዮጵያዊ) ዜግነቱን በራሱ ፈቃድ እንደተወ ይቆጠራል” ይላል። ስርዝና ቅንፍ የኔ። “በራሱ ፍላጎት” የሚለው አባባል በዲቪ ወይም በሌላ ሕጋዊ በሆነ ዘዴ ካገር ወጥተው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የሚኖሩበት አገር ሕግ በሚፈቅደው መሰረት የዜግነት ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልተው የሌላ አገር ዜግነትን የወሰዱትን ብቻ ሳይሆን በፖሊቲካ ምክንያት ሳይፈልጉ በግድ ካገር ተሰደው በሌላ አገር ጥገኝነት ጠይቀው “የስደተኛ መብት” ያገኙና ከጊዜ ባኋላ ጥገኝነት የጠየቁበትን አገር ዜግነት የወሰዱትን ትውልደ ኢትዮጵያውያንንም ያጠቀልላል። ተገዶ የውጭ አገር ዜጋ የሚሆን የለምና!

በራሳቸው ፍላጎት ሳይሆን በሌላ ምክንያት የሌላን አገር ዜግነትን ላገኙ ለምሳሌ፣ ከትውልደ ኢትዮጵያውያን (ወይንም ከኢትዮጵያውያን ዜጎች) ወላጆች በአሜሪካን ምድር ላይ በመወለዳቸው ብቻ የአሜሪካን ዜግነትን ያገኙትን ግለሰቦች በተመለከተ፣ የኢትዮጵያ የዜግነት ሕግ በአንቀጽ 20(3) ላይ የሚከተለውን ያስቀምጣል። “ራሱ ጠይቆ ሳይሆን በማናቸውም ሌላ ምክንያት ተመሥርቶ በሕግ ድንጋጌዎች ተፈጻሚነት የተነሳ የሌላ አገር ዜግነት ያገኘ ኢትዮጵያዊ፣

ሀ) ባገኘው የሌላ አገር ዜግነት መብቶች መጠቀም ከጀመረ ወይም፣

ለ) በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ያገኘውን የሌላ አገር ዜግነት ትቶ በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ ለመቀጠል መምረጡን ለባለሥልጣኑ ካላሳወቀ ዜግነቱን በፈቃዱ እንደተወ ይቆጠራል” ይላል።

በሌላ በኩል ደግሞ፣ የሌላ አገር ዜግነትን የወሰዱትን ትውልደ ኢትዮጵያውያንን መልሶ ለማቀፍና ባገሪቷ የፖሊቲካም ሆነ ማህበራዊው ዘርፍ በሰላም እንዲሳተፉ ከማሰብ አንጻር በአንቀጽ 22 ውስጥ የሚከተለውን ቅድመ ሁኔታ አካትቷል።

“አስቀድሞ ኢትዮጵያዊ የነበረና በሕግ የሌላ አገር ዜግነት ያገኘ ሰው፣

ሀ) ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በመምጣት መደበኛ መኖርያውን በኢትዮጵያ ውስጥ ከመሠረተ፣

ለ) ይዞት የነበረውን የሌላ አገር ዜግነት ከተወ እና፣

ሐ) ዜግነቱ እንዲመለስለት ለባለሥልጣኑ ካመለከተ የኢትዮጵያን ዜግነት መልሶ ሊያገኝ ይችላል።

እነዚህ የሕግ አንቀጾች ወደ ቀላል አማርኛ ሲተረጎሙ፣

ሀ) በተለያየ ምክንያት የኢትዮጵያን ዜግነት ትተው የሌላ አገር ዜግነት የወሰዱ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ የተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ካሟሉ፣ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰው የኢትዮጵያዊነት ዜግነታቸውን መልሰው ለማግኘት ይችላላሉ። ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ሕጉን ተከትለው፣ የውጪ ዜግነቱን አስረክበውና፣ ማስረከባቸውንም የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከማመልከቻቸው ጋር አያይዘው ለኢትዮጵያ የደህንነት የኢሚግሬሽንና የስደተኞች ጉዳይ ባለሥልጣን ማስረከብ አለባቸው ማለት ነው። የኢሚግሬሽንና የስደተኞች ጉዳይ ባለሥልጣንም ጉዳዩን ለኮሚቴ አቅርቦ እስኪያስጸድቅላቸው ድረስ ግን፣ እንደ ትውልደ ኢትዮጵያዊ በሕግ በተሰጣቸው መብት መሠረት እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖርና ከፖሊቲካ ውጭ በሆነ ማንኛውም የሥራ መስክ ተሰማርተው አገራቸውን ማገልገል ይችላሉ። (የዚህ ኮሚቴ ሰብሳቢ የኢሚግሬሽን ባለሥልጣን ሲሆን፣ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከፍትህ ሚኒስቴር እና ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተውጣጡ አንዳንድ አባላት ይኖሩታል)

እነዚህን የሕግ ቃላት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ከሚፈልጉት ትውልደ ኢትዮጵያውያን የወደፊት የኢትዮጵያ ቆይታቸውና ብሎም በኢትዮጵያ ፖሊቲካ ውስጥ ሊኖራቸው ከሚችለው ዕውኔታ ጋር ለማጣጣም፣ እንደገና ወደ ኢትዮጵያ ዜግነት ሕጋችን መመለሱ ግድ ይላል።

ኢትዮጵያ የጣምራ ዜግነትን ሕጋዊ መብት አትፈቅድም፡፡ ስለሆነም ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሌላ አገር ዜጋ ሆነው እያለ የኢትዮጵያም ዜጋ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ የውጭ አገር ዜግነትን አስረክበው ኢትዮጵያዊ ለመሆን ለሚሹ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይህ እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ የጣምራ ዜግነትን ጉዳይ የሚያጠና ቡድን በቅርቡ ሥራውን እንደሚጀምር ዶ/ር ዓቢይ ከተናገሩ ዓመት ቢሆነውም እስከዛሬ ድረስ ጥናቱ ምን ላይ እንደደረሰ የሚያሳይ ፍንጭ የለም፡፡ ያ ተግባራዊ እስካልሆነ ድረስ ደግሞ፣ ለምሳሌ የአሜሪካንን ዜግነትን ለመተው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ለአሜሪካን ኤምባሲ ማሳየት ከሚገባቸው ዶኩሜንቶች አንዱ የሆነው “ሁለተኛ የሌላ አገር ፓስፖርት” ስለሚጎድልና፣ ቆንሲሉ የሌላ አገር ዜግነት ማረጋገጫ የሆነውን ተጨማሪ ፓስፖርት በዓይኑ ካላየና ኮፒውን በእጁ ካላስገባ፣ አመልካቹን ማሰናበት ለ“ዜግነት አልባነት” ማጋለጥ ስለሚሆንበት ማመልከቻውን ለማስተናገድ ይቸግራል፡፡ ታዲያ መፍትሄው ምንድነው? ለጊዜው አጥጋቢ መልስ ባይኖረኝም፣ ተፈጻሚ የመሆን ዕድል ይኖራቸዋል ብዬ የምገምታቸውን ሁለት ሁኔታዎችን ግን መጠቆም እችላለሁ፡፡ የመጀመርያው፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊው የውጭ አገር ዜጋ “ለኢትዮጵያ ከፍተኛ አስተዋዖ ያበረከተ” መሆኑ ከታመነበት ምንም እንኳ በሕጉ የተካተቱትን ቅድመ ሁኔታዎችን ባያሟላም በኢትዮጵያ የዜግነት ሕግ አንቀጽ 8 መሠረት አመልክቶ ዜጋ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ግን መንግሥት እንዳስፈላጊነቱ ለሚያስፈልገው ግለሰብ የሚሠጠው “ችሮታ” እንጂ ሕጋዊ መብት ስላልሆነ የመሳካት ዕድሉ የጠበበ ይመስለኛል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ የጣምራ ዜግነትን አስፈላጊነት ሕዝብን አሳምኖ፣ የዜግነት ሕጉን ማሻሻል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለ ዜግነት ያለው ትልቅ ግምትና በተለይም “ኢትዮጵያዊነታቸውን ትተው የውጪ ዜጋ ስለሆኑ” ትውልደ ኢትዮጵያውያን (እኔንም ጨምሮ) ያላቸውን የቅሬታ መንፈስ ሳስብ፣ ሕገ መንግሥቱን አሻሽሎ ጣምራ ዜግነትን የመፍቀዱ ጉዳይ በቅርቡ ተግባራዊ ይሆናል የሚል ግምት የለኝም፡፡

(ጸሃፊው ቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣን የነበሩ የዓለም አቀፍ ሕግ ባላሙያ ናቸው፡፡) ጄኔቫ፣ ጥር 13 ቀን 2020 ዓ/ም

wakwoya2016@gmail.com
+++++++++++++
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።

http://www.goolgule.com/changing-ones-nati

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.