Breaking News
Home / Amharic / ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የብሔራዊ ምክር ቤት የ1ኛ ዓመት 4ኛ መደበኛ ጉባዔ ማጠናቀቂያ የተሰጠ መግለጫ

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የብሔራዊ ምክር ቤት የ1ኛ ዓመት 4ኛ መደበኛ ጉባዔ ማጠናቀቂያ የተሰጠ መግለጫ

**
የአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል በአፈና አይገታም !

የህዝባችን ሁለንተናዊ ትግል አምጦ የወለደው አብን የአማራ ህዝብ መሰረታዊ የኅልዉና፣ የፍትኅና የእኩልነት ጥያቄዎችን በመለየትና አማራዉን በማደራጀት የተጋረጠበትን የኅልውና አደጋ በመቀልበስ ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር በእኩልነትና በፍትኃዊነት የሚኖርባትን ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ በሰላማዊ መንገድ እየተንቅሳቀሰ ያለ ድርጅት ነዉ፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ብሔራዊ ምክር ቤት ከነሃሴ 11-12/2011 ዓ.ም ሲያካሂድ የቆየውን የ1ኛ ዓመት 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮችን፤ የንቅናቄውን የአንድ ዓመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርትና የቀጣይ ዓመቱን እቅድ ገምግሞ በማጽደቅ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል።

1. ሰኔ 15 ቀን 2011ዓ.ም በአማራ ሕዝብ መሪዎችና የአገሪቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ላይ የተፈፀመው አጠቃላይ ሕዝባችንና ድርጅታችን ያሳዘነ አስነዋሪ ግድያ በገለልተኛ አጣሪ ቡድን ተጣርቶ፤ በዚህ ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉ አካላት ለሕግ እንዲቀርቡና ፍትኅ እንዲሰጥ እንጠይቃለን፡፡

2. የአማራ ሕዝብ መሪዎችን ግድያና “በክልሉ” ያለውን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ በመጠቀም በድርጅታችን አመራሮች፤ አባላትና ደጋፊዎች ላይ የሚደረገው መጠነ ሰፊ እስራት፣ ወከባና መንግስታዊ እገታ ምክር ቤቱ አጥብቆ ያወግዛል፡፡ ይህ ጉዳይ ኢ-ፍትሃዊ የሆነ፣ የፖለቲካ ሸፍጥ ያለበት፣ ለሀገር ግንባታ የማይጠቅምና የፓርቲዎችን የቃልኪዳን ስምምነት በጣሰ መልኩ እየተከናወነ ያለና ኃላፊነት የጎደለው የመንግስት ድርጊት ነው፡፡ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትም ጉዳዩ ትክክል እንዳልሆነ በመግለፅ አጋርነቱን ያሳየ ቢሆንም ገዢው ፓርቲና እርሱ የሚመራው መንግስት በማን አለብኝነት የገባውን ቃልኪዳን ስምምነት ችላ በማለት የንቅናቄያችንን ሰላማዊ ትግል እያወከው ይገኛል። በፓርቲዎች መካከል የተደረሰዉ ስምምነት በገዢዉ ፓርቲ የማይከበር ከሆነ ንቅናቄያችን ከፓርቲዎች ም/ቤት ራሱን እንዲያገል ብሔራዊ ምክር ቤቱ ይሁንታዉን በመስጠት፤ በቀጣይ የመንግስት ምላሾች እየታዩና እየተገመገሙ መወሰድ ስላለባቸው የሰላማዊ ትግል ስልቶች አቅጣጫ አስቀምጧል። መላው የአማራ ሕዝብም ይህንን በሚመለከት አብን በየጊዜው የሚያደርጋቸውን ጥሪዎች በአንክሮ እየተከታተለ በማናቸውም ሁኔታ ከልጆቹ ጎን እንዲሆንና መብቱንና ጥቅሙን ለማስከበር የሚደረገውን ትግል ከፍ እንዲያደርገው ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

3. አማራ «ክልል» ተብሎ ከሚጠራዉ አካባቢ ዉጭ በሚኖሩ አማሮች፣ የአሥራት ቴሌቭዥን ጋዜጠኞች ፣ የአማራ ፀጥታና ደህንነት ከፍተኛ አመራሮችና የአማራ ሕዝብ የመብት አንቂዎች ላይ የሚደረገው እስርና ወከባ የአማራ ጠልነት መንፈስ ቅጥያ መሆኑን አብን ይገነዘባል። ስለሆነም መንግስት የአማራን ድምፅ ለማፈን እየሄደበት ያለውን ያልተገባና ኋላቀር አካሄድ እንዲያቆም እያሳሰብን ጋዜጠኞች፣ የበጎፈቃድ አገልጋዮች፣ የፀጥታ መሪዎችና የአማራ ህዝብ የመብት አንቂዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እየጠየቅን መላው ህዝባችንም በሚዲያው ላይና በልጆቹ ላይ እየተደረገ ያለውን የአፈና ሸፍጥ በአንክሮ እንዲከታተልና ከልጆቹ ጎን እንዲቆም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ፡፡

4. ም/ቤቱ በአንድ ዓመት ውስጥ የተሠሩ የፖለቲካ ሥራዎች ስኬታማ ቢሆኑም በቀጣይ የአብንን ተቋማዊ አቅም በማጠናከር የትግላችን ግለት የበለጠ ለመጨመር በሚከተሉት ጉዳዮች ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባው የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።

– በቀጣይ በመላ ሀገሪቱ በተለይም በገጠር የሚኖረውን ሰፊውን የአማራ ህዝብ ተደራሽ ለማድረግና የአብን ሀሳብ እንዲቀነቀን በትኩረት መሠራት እንደሚገባው አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

– በውጭው ዓለም የሚኖረውን አማራ በተጠናከረ መልኩ በማደረጀት የአብንን እንቅስቃሴ በባለቤትነት እንዲደግፉና ሁለንተናዊ ተሳትፎና አበርክቶአቸውን በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ እንዲወጡ ምቹ ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጧል። በመሆኑም በመላው ዓለም የምትኖሩ አማራዎች ከምንጊዜውም በላይ የአማራ መተባበርና መተጋገዝ የሚያስፈልግበት ጊዜ መሆኑን በመረዳት ከአብን ጎን በመሰለፍ የሕዝባችን የኅልውና ትግል እንድታጠናክሩ ከወዲሁ የከበረ ጥሪያችን እናስተላልፋለን።

– የአማራ ሕዝብ ጥቅሞችና ፍላጎቶችን የሚከብረው ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በሚደረግ የፖለቲካ ውይይትና ድርድር መሆኑን እንገነዘባለን። በዚህ በኩል የተጀምሩ አበረታች ሥራዎች ቢኖሩም በቀጣይ ለሕዝባችን የጋራ ጥቅም መከበር የአብረን እንሥራ ንግግሮችም ግልፅ በሆነ መልኩ በሰነድ የተደገፉ እና የአማራን ሕዝብ ጥቅም ባስከበረ ሁኔታ ብቻ የሚፈፀሙ መሆኑ ታውቆ መከወን እንዳለባቸው አቅጣጫ ተቀምጧል።

– አብን በቀጣይ ዓመት በሚደረገው ምርጫ በመወዳደር ሕዝባችንን በወርዱና በቁመቱ እንዲወከል ለማስቻል በሚያደርገው ፖለቲካዊ ትግል ሙሉ አቅሙን የሚጠቀም ሲሆን ለዚህም የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶች አስቀድመው መከናወን እንዳለባቸው ብሔራዊ ም/ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል።

በመጨረሻም መላው የአማራ ሕዝብ፤ የድርጅታችን አመራር፣ አባላትና ደጋፊዎች የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል የሚደመደመው በድል መሆኑን በመገንዘብ ከወትሮው በተሻለ በንቃት እንድትሳተፉና ከድርጅታችሁ አብን ጎን እንድትሰለፉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ፡፡

አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ !!!

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ብሄራዊ ምክር ቤት

ነሃሴ 13 ቀን 2011 ዓ/ም
አዲስ አበባ ፣ ሸዋ

One comment

  1. Minweyelet Kassa

    Keep Strong ! We will WIN ! Watch & take measures for those(Banda) working for TPLF and OLF .

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.