ጋዜጠኛና የሠብአዊ መብት ተሟጋች የነበረው እስክንድር ነጋ ብዙ ዋጋን የከፈለ ፣ የምናከብረውና በግለሰባዊ ስብእናውም አዛኝ ፣ ትሁት ፣ ቅንና ለቃሉ ሟች የሆነ ኢትዮጵያዊ ወንድማችን ነው። በዚሁ ሙያውና ምግባሩ ቢቀጥልና ከከፍታው አይወርድም የሁላችንም ደስታ ነበር።
ነገርግን ከእስር ከተፈታ በኃላ በጋዜጠኛና የሠብአዊ መብት ተሟጋችነቱ ብሎም በከፈለው መራር ዋጋ ያገኘው የህዝብ ድጋፍና እውቅና በፖለቲካውም የሚቀጥል መስሎት በአንዳንድ ግለሰቦች ጉትጎታ ጭምር ህይወቱን ከአደባባይ ወደ እስር ቤት ከእስር ቤት ወደ አደባባይ ወዳደረገው ፖለቲካ ከገባ በኃላ የሚያደርጋቸው ተግባራትም ሆኑ የሚከፍለው መስዋዕትነት የጤናውን ሁኔታ ሁሉ አጠያያቂ የሚያደርጉ እየሆኑ ነው።
ብሄራዊ በአል በተከበረ ቁጥር ባንዲራ እየያዙ እንገፍ እንገፍ ማለትና ከፀጥታ አካላት ጋር እየተጋጩ መታሠር ጀግንነትም ሆነ ህዝብ የሚፈልገው ትግል አይደለም። እስክንድር በጣም ይሉኝታ የሚያጠቃው ሰው ስለሆነ መንጋ ደጋፊዎች የሚያራምዱትን ፍላጎት ካልፈፀመ ቃሉን የበላ ይመስለዋል። ለዚያም ነው በቅርቡ እንኳ ጥቂት ከጎኑ ከማይጠፉ አጃቢዎቹ ጋር አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ይዞ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በመሄድ ከፀጥታ አካላት ጋር ያደረገውን ግብግብ በቪዲዮ ቀርፆ ‘ይኸው በቃሌ መሠረት ባንዲራ ይዤ ቦሌ ተገኝቻለሁ!’ ሲል ለመንጋ ደጋፊዎቹ ያስተላለፈው። በቃ ትግሉ በዚህና በመሠል መሠረታዊ ያልሆኑ ጉዳዮች ላይ የተጣበቀ እለት ተእለት ከፀጥታ አካላት ጋር በሚደረግ አምባጓሮ ላይ የተወሠነ ነው።
ማንነቴ ከአማራነት ይልቅ በኢትዮጵያዊነት የሚገለፅ ነው ብሎ የሚያምነውና የአማራን ስም ከያዙ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ከመቆም ይልቅ በአዲስአበባ ዙሪያ የተወሠነ ፓርቲ የመሠረተው እስክንድር ፣ አዲስአበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነች እያለ የሚመሠክረው ስክንድር የፖለቲካ መሠረቱን ግን የአማራን ህዝብና ክልል አድርጎ አክሳሪ ፖለቲካ እንደሚሠራ እንኳ አይረዳውም። የአማራን ፖለቲካ ጭምር ከማዳከም ጀምሮ ህዝቡ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች አይን በስጋት እንዲታይ ማድረጉንም አያሰላስለውም። አማራ ክልል በየወረዳው እየዞረ ‘ዝዋይ አማራ ነው ናዝሬት የአባቶቻችን ‘ አይነት ፖለቲካሊ ሮንግ የሆነ ባነር አሰርተው ከሚያጅቡት መንጋ ደጋፊዎች ጋር ትርፍ አልባ ቱር ከሚያደርግ በኦሮሚያ ክልል ፣ በሲዳማ ክልል ፣ በደቡብ ክልል ፣ ….ወዘተ ተንቀሳቅሶ የህዝብ ለህዝብ ትስስር የሚያጎሉና የሚያቀራርቡ ዝግጅቶችን ቢያደርግ ለአማራውም ለኢትዮጵያም ጥሩ ውጤት የሚያመጣ ፖለቲካ እንደሚሠራ እንኳ አይረዳውም። በቃ የደጋፊን ጭብጨባ ተከትሎ መንጎድ ፣ የህዝቡ ተቀዳሚ አጀንዳ ባንዲራ ይመስል በእንጨት ሁለት ሶስት ሰንደቅ አላማ ይዞ በየአደባባዩና መስሪያ ቤቱ ግብግብ መግጠም መታሠር መፈታት ብቻ።
አሁንም በቅንነት ‘እስክንድር ፖለቲካ ለአንተ አይሆንም! በቃህ!’ የማይሉት መንጋዎች በአማራ ክልል ከመደረገው ጉብኝት በኃላ ለምን ፓርቲህን አገርአቀፍ አድርገህ አማራ ክልልም አትንቀሳቀስም? ብለውት ይሄው ሌላ የአማራን ፖለቲካ ጭምር የሚጎዳ ዝግጅት ጀምሯል።
ኧረ ባካችሁ ውዱ ወንድማችንን በቅንነት ምከሩት!