SHARE!
- ዋዜማ ራዲዮ የስምምነት ረቂቅ ሰነዱን አግኝታለች
ዋዜማ ራዲዮ- በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሀ አሞላልና የድርቅ ማካካሻ ላይ የኢትዮጵያ : የሱዳንና የግብጽ የውጭና የውሀ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከህግና የቴክኒክ ባለሙያዎቻቸው ጋር ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ ዋሽንግተን ካደረጉት ውይይት በሁዋላ ከመቀራረብ ላይ ስለመድረሳቸው ከሁሉም ወገኖች ተሰምቷል።
አሜሪካና የአለም ባንክ በአደራዳሪነት በተገኙበት ይህ ስብሰባ የሶስቱም ሀገራት የውሀና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በውሀ አሞላልና ድርቅ ማካካሻ ሰነዱ ላይ በፈረንጆቹ የፊታችን የካቲት 13 2020 (Feb 13, 2020) ይፈርማሉ ተብሎ ይጠበቃል በፈረንጆቹ የካቲት 28 2020 (Feb 28, 2020) ደግሞ በመሪዎች ደረጃ ፊርማ ያኖራሉም ተብሏል።
አሁን ላይ የውሀና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ወደየሀገራቸው ቢመለሱም የቴክኒክና የህግ ባለሙያዎቹ እዚያው ዋሽንግተን ይገኛሉ። እስከ ፊርማው ማጠናቀቂያም እዚያው ይቆያሉ። የኢትዮጵያ የቴክኒክና የህግ ባለሙያዎችም እዚያው ዋሽንግተን እንደሚገኙም ማረጋገጥ ችለናል። መንግስትም ስምምነቱ እንዲፈረም ፍላጎት እንዳለው ሰምተናል።
ዋዜማ ራዲዮ ያገኘችው ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሞላልና ድርቅ ቢከሰት ማካካስ እንዲቻል በሚል እንዲፈርሙበት የተዘጋጀው ረቂቅ የስምምነት ሰነድ፣ ኢትዮጵያን ቋሚ የውሀ ባለ እዳ የሚያደርግ መሆኑን መረዳት ችለናል። በዚህ ረቂቅ ስምምነት ላይ ሁለት የኢትዮጵያን ጥቅም አደጋ ውስጥ የሚጥሉ ይዘቶች እንዳሉ ዋዜማ ራዲዮ ሰነዱ ላይ ከባለሙያዎች ማብራሪያን አግኝታለች። ሁለቱም አደጋዎች ያሉት ድርቅ ፣ ተከታታይ ድርቅና ረጅም ዝናብ አጠር አመታት ቢከሰቱ የሚደረገው ማካካሻን የተመለከተው የሰነዱ አካል ላይ ነው።
አንዱ ጉዳይ ፣ ድርቅ ቢከሰት ከአባይ ውሀ ለግብጽ እንዲለቀቅ የሚጠበቀው ውሀ ወደ ህዳሴው ግድብ ከሚገባው ውሀ እንዲሆን ሲገባው ረቂቅ ሰነዱ ግን ይህን አይጠቅስም። የሚለቀቀውን ውሀ በቁጥር ከማስቀመጥ ውጭ። እዚህ ጋር ” ግብጽ ድርቅ አጋጠመኝ ብትል ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ከያዘችው ውሀ ውጭ ከየት አምጥታ ነው ለግብጽ ማካካሻ የምትለቀው ? ” የሚል ጥያቄን ያስነሳል። ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ በግድቧ ላይ ውሀ ትያዝ አትያዝ ከግንዛቤ ሳያስገባ የውሀ ባለዕዳ የሚያደርጋት መሆኑን ባለሙያዎች ያሰምሩበታል።
ምናልባትም ይህ የሰነዱ አካል ኢትዮጵያ የአባይን ውሀ ከግድቡ ውጭ ከአሁን በሁዋላ ለምንም እንዳታውል ለማገድ ያለመ ነው።
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሶስቱ ሀገራት እንዲፈርሙ የተዘጋጀው ሰነድ ድርቅን ስለማካካስ ቢያወራም ድርቅ ግብጽ ውስጥ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚከሰት ከግምት ውስጥ አያስገባም። ይህም ግብጽ ድርቅ አጋጠማትም አላጋጠማት ያለምንም ገደብ የማካካሻ ውሀ ይለቀቅልኝ ብላ እንድትጠይቅ መንገድን የሚከፍት ነው። ኢትዮጵያን ግን ድርቅ ውስጥ ብትሆን እንኳ ስለራሷ ሳይሆን ስለ ግብጽ ድርቅ እንድታስብ የሚያስገድዳት ነው። ይህ በአለማቀፍ ህግ እንኳ የማይታሰብ ነው።
” ኢትዮጵያ በዚህ ደረጃ በውሃዋ የማዘዝ መብቷን የምታጣ ከሆነ ታድያ ግድቡን ሲጀመር መገንባት አያስፈልጋትም ነበር ” ብለውናል አንድ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው እዚያው ዋሽንግተን የሚገኙ ባለሙያ። እነዚህ ሁለት ጉዳዮች የኢትዮጵያን ጥቅም በእጅጉ አደጋ ውስጥ የሚጨምሩ የረቂቅ ስምምነቱ አካላት ናቸው ያነጋገርናቸውና ለጉዳዩ እጅግ ቅርብ የሆኑ ባለሙያዎች እንደሚያስጠነቅቁት።
ስለ ድርቅ የሚያወራው የረቂቅ ስምምነቱ ክፍል በዋነኝነት ሁለት ምእራፎች አሉት ። በመጀመርያ ጊዜ ሙሌት እና በረጅም ጊዜ ኦፕሬሽን ድርቅ ቢከሰት ኢትዮጵያ የምትለቀውን የውሀ መጠን በመቶኛ አስቀምጧል። የተቀመጡ ቁጥሮች ውስብስብና አላስፈላጊ ግዴታዎች ውስጥ ኢትዮጵያን ሊያስገቡ የሚችሉ ናቸው ።
ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ለመጀመርያ ጊዜ በ4.5 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ የመሙላት እቅድ ነው ያላት።በዚህ ጊዜ ድርቅ ተከሰተ ከተባለ ይሄ ውሀ የሚሞላበት ጊዜ እንዲቀየር ረቂቅ ሰነዱ ያስቀምጣል። ድርቅ ማለት “የአባይ ውሀ አመታዊ ፍሰት 31 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ሲሆን ነው” በሚል ተቀምጧል። ከህዳሴ ግድብ በእየአመቱ መለቀቅ ያለበት ደግሞ 37 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ መሆኑም ተጠቅሷል።
እዚህ ጋር ሁለት አደገኛ ድንጋጌዎችን በምሳሌነት ማንሳት ያስፈልጋል።አንዱ ግድቡ ለመጀመርያ ጊዜ በሚሞላበት ጊዜ ለአራት ተከታታይ አመታት ከህዳሴው ግድብ የሚለቀቀው ውሃ ከ37 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ዝቅ የሚል ከሆነ ኢትዮጵያ ከዚያ በሁዋላ ለሚቀጥሉት አራት አመታት ከግድቡ የባህር ጠለል ከ603 ሜትር በላይ ካለው ውሃ 62.5 በመቶውን ትለቃለች ይላል።የህዳሴ ግድብ ከባህር ጠለል በላይ 603 ሜትር ላይ ሲደረስ 25 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ ይዟል ማለት ነው። ይህም ማለት ግድቡ 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ ካለው 30.6 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀን ለአራት አመታት ከፋፍላ ትለቃለች ማለት ነው። በየአመቱ የሚለቀቀው ውሀ ሳይጨመር ማለት ነው።
ኢትዮጵያ 30.6 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ማካካሻ ውሀውን ለአራት አመታት ለመልቀቅ ግዴታ ውሰጥ ስትገባ ሊያጋጥማት የሚችለውን የውሀ እጥረት እንኳ ከግምት ውስጥ ሳታስገባ ፣ እንዲሁም በተጠቀሰው አመት ውሀውን ከዝናብ ታግኘው አታግኘው ሳይታይ እንደሆነ በረቂቅ የስምምነት ሰነዱ ተቀምጧል።
በሌላ በኩል በግድቡ የረጅም የኦፕሬሽን ጊዜ ለአራት አመታት ከህዳሴው ግድብ የለሚቀቀው ውሀ ከ39 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ በታች ከሆነ ኢትዮጵያ ከህዳሴው ግድብ ከባህር ጠለል 603 ሜትር በላይ ያለውን ውሀ ሙሉ ለሙሉ ለአራት አመታት ከፋፍላ እንድትለቅ ይጠበቃል።ይህ ማለት ግድቡ 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ ቢኖረው እስከ ባህር ጠላል በላይ 603 ሜትር ያለውን 25 ቢሊየን ሜትር ኩዩብ ውሀ ቀንሳ 49 ቢሊየን ሜትር ኪዩቡን ለቀጣይ አራት አመታት ከፋፍላ ትለቃለች እንደማለት ነው። ይሄ ሊገባ የሚችለው ግዴታም ታድያ ኢትዮጵያ ውሀውን በነዚህ ጊዜያት እንድታገኝታ ምቹ የአየር ሁኔታ ይኑር አይኑር ከግምት ውስጥ ሳይገባ ነው።
ዐልቦ ዘመድ ኢትዮጵያ
አሜሪካና የኣአለም ባንክ የህዳሴውን ግድብ ጉዳይ አደራዳሪ ሆነው ብቅ ማለታቸው ሳያንስ ባለፈው ሳምንት በተደራዳሪዎች ላይ ያሳደሩት የማስገደድ ጫና በግልፅ ለግብፅ መወገናቸውን ያሳየ እንደነበር ከተደራዳሪዎች ሳይቀር ሰምተናል። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ባለፈው ሳምንት ስልክ ደውለው ኢትዮጵያ ስምምነቱን እንድትፈርም በዚህም የአሜሪካ ወዳጅነቷ እንደሚቀጥል አስረግጠው መናገራቸውን ስምተናል። ለኢትዮጵያ ከአለማቀፍ አበዳሪዎች ቃል የተገባላትና ከአሜሪካ የምታገኘው ድጋፍ ይህን ስምምነት ካልፈረመች መስተጓጎል ሊገጥመው እንደሚችል ሌሎች የአሜሪካ መንግስት የበታች ባለስልጣናት ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በገምዳሜ መጠቆማቸው አልቀረም።
በስልክ ንግግሩ ወቅት ስምምነቱን ለመፈረም እንደሚቸገሩ የገለፁት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ጉዳዩን ከባለሙያዎች ጋር እንደሚመክሩበት ሲገልፁም ተሰምተዋል።
አሁን ግን ስምምነቱን ወደ መፈረሙ እንዳዘነበሉና ድንገትም ከፍተኛ የመንግስት ልዑካን ወደ ዋሽንግተን እንደሚያቀና ፍንጮች አሉ።
ብዙ ባለሙያዎችና ሀገር ወዳድ ዜጎች የህዳሴው ግድብ ስምምነት ለህዝብ ይፋ ተደረጎና በይፋ ተመክሮበት አቋም ቢወሰድበት የተሻለ መሆኑን ነግረውናል። በራሳችን ህዝብ ገንዘብ ለምንገነባው ግድብ ባለቤትነታችንን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ስምምነት እንድንፈርም መገደዳችን በሉዓላዊነታችን ላይ ቀጥተኛ አደጋም አስከትሏል ብለው የሚያምኑ አሉ።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለመካከለኛው ምስራቅ (ፍልስጤምና እስራኤል) ያቀረቡት የሰላም ሀሳብ በመላው የዓረቡ አለም ተቀባይነት ባለማግኘቱ የዓረቡ አለም ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነችው ግብፅ የዓረብ ሀገራትን እንድታግባባ ይፈልጋሉ። ለዚህም ውለታዋ የህዳሴ ግድብ እንደ እጅ መንሻ ቀርቧል። አንድ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ያለፈው ሳምንት ውይይት ማብቂያ ላይ እንደነገሩን ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ላይ “ብቻዋን ቆማለች (አልቦ ዘመድ) ሆነናል”
To contact Wazema editors wazemaradio@gmail.com