የአዲስ አበባን ሕዝብ መብትና ፍላጎት በጉልበት ለመጨፍለቅ የሚደረገው እንቅስቃሴ በአስቸኳይ ይቁም!
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ /ኢዜማ/ የተሰጠ መግለጫ፤
ባለፈው ዓመት ታህሳስ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቂሊንጦ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጀምሮ እስከ ትናንትናው ህዳር 28 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ በበርካታ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ፣ የክልል መለያ አርማና መዝሙርን መነሻ በማድረግ አላስፈላጊ ውጥረትና ግጭት እንዲቀሰቀስ እና የትምህርት ሂደቱ እንዲስተጓጎል ተደርጓል፤ ሁኔታውም እየተባባሰ ሊሄድ እንደሚችል የሚያሳዩ በርካታ ምልክቶችም አሉ።
ሰንደቅ ዓላማ እና ብሔራዊ መዝሙር የሀገርን ትርጉም የሰነቁ ትዕምሮቶች ናቸው። ጀግኖች አባቶቻችን ቀኝ ገዢ ወራሪዎችን የተፋለሙት የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ አንግበው፤ ብሔራዊ መዝሙሯንም በሕብረት እየዘመሩ ስለመሆኑ ታረክ በደማቁ መዝግቦታል። አትሌቶቻችን ድል ባደረጉባቸው የዓለም አደባባዮች ሁሉ በድል ከፍ አድርገው ያውለበለቡት የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ ነው። በስሜት እንባቸውን አፍስሰው የዘመሩትም ብሔራዊ መዝሙራችንን ነው። በአሸባሪዎች የተከፈተብንን ጦርነት የመከትነውም በሀገራችን ሰንደቅዓላማ ስር ተሰባስበን ነው። ይህ ሁሉ የሚያመለክተው ሰንደቅዓላማ እና ብሔራዊ መዝሙር የሀገር መገለጫ ክቡር ጌጦች መሆናቸውን ነው።
ከዚህ መሠረታዊ ግንዛቤ፣ መርህ እና ሕጋዊ አሠራር ባፈነገጠ መልኩ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚደረገው ሕገወጥ የሆነ የአንድን ክልል መዝሙር እና መለያ አርማ ከሀገር ሰንደቅ ዓላማ እና ብሔራዊ መዝሙር እኩል ወይም በላይ ተማሪዎች ላይ ለመጫን መሞከር ግጭትና ሁከትን ወደ ከተማዋ ማስረግ መታሰቡን ማሳያ ነው፡፡
ኢዜማን ግርታ የፈጠረበት ጉዳይ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የተቀመጡ የአዲስ አበባ አስተዳደር እና የፌደራል መንግስት ሀላፊዎች በጉዳዩ ላይ ያላቸው አረዳድ ትክክለኛ ባለመሆኑ መሬት ላይ እየፈጠሩት ያለውን ችግር ልብ ብለን ስናየው ችግር ካልተፈጠረ በሥልጣን ላይ መቆየት የማይችሉ እስከሚመስል የተደረሰበት ሁኔታ ነው። አንድን አመለካካት ብቻ በበላይነት ለመጫን የተቀረፀው ሕገ መንግስት እንኳን በሁኔታው ላይ ከሚሰጠው አረዳድ ውጭ በአዲስ አበባ ከተማና በኦሮሚያ ክልል መሀከል ያለውን የግንኙነት መስመርና የአሰራር መርህ የጣሰ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከተለያዩ ምንጮች ያሰባሰባቸው መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ይህ ሕገወጥ ተግባር በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በተከታታይ ተስተውሏል። ለአብነትም፤
አርብ ታህሳስ 22 ቀን 2014 ዓ.ም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቂሊንጦ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፤
ረቡዕ ሚያዚያ 26 ቀን 2014 ዓ.ም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ብሔራዊ አፀደ ህፃናት እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፤
ረቡዕ ግንቦት 17 ቀን 2014 ዓ.ም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ገላን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤
ረቡዕ ሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም በየካ ክፍለ ከተማ በሚገኘው በሚያዝያ 23 የአጸደ ህጻናት እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፤
ሐሙስ ጥቅምት 2 ቀን 2015 ዓ.ም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፈለገ ዮርዳኖስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤
ማክሰኞ ጥቅምት 8 ቀን 2015 ዓ.ም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጠመንጃ ያዥ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤
ሐሙስ ህዳር 22 ቀን 2015 ዓ.ም በጉለሌ ክፍለ ከተማ እንጦጦ አምባ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤
አርብ ህዳር 23 ቀን 2015 ዓ.ም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ድል በትግል እና አዲስ ተስፋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፤
ማክሰኞ ህዳር 27/2015 ዓ.ም ጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 10 ሙሉ ብርሃን (አዲስ ብረሃን) ትምህርት ቤት፤
ማክሰኞ ህዳር 27/2015 ዓ.ም ጉለሌ ክ/ከተማ ቀጨኔ ደብረሰላም ትምህርት ቤት፤
ማክሰኞ ህዳር 27/2015 ዓ.ም የካ ክ/ከተማ ከፍተኛ 12 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤
ረቡዕ ህዳር 28/ 2015ዓ.ም በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ አዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤
በእነዚህ ትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ክልልን አርማ ለመስቀል እና የክልሉን መዝሙር ለማስዘመር በተደረጉ ሕገወጥ ተግባራት ረብሻዎች፣ ግጭቶች እና የትምህርት ክፍለጊዜ መስተጓጎሎች ከመከሰታቸውም ባለፈ ድርጊቱን የተቃወሙ ተማሪዎች እና መምህራንም ታስረዋል፤ ተደብድበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች አንድም በከተማው አስተዳደር ወይም በፌደራል መንግስቱ ሥር ያሉ ናቸው። የአዲስ አበባን መስተዳደር ም/ቤትን የመረጠው የአዲስ አበባ ሕዝብ እንጂ የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ አይደለም፤ የፌደራል መንግስቱም የተመረጠው፣ የአዲስ አበባን ሕዝብ ጨምሮ፣ በሁሉም ክልሎች በሚኖረው ሕዝብ በመሆኑ፣ በአዲስ አበባ አስተዳደር ወይም በፌደራል መንግስት ሥር የሚገኙ ት/ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎችን የኦሮሚያ ክልል መዝሙር ዘምሩ፣ የክልሉን ሰንደቅ ዓላማ አውለብልቡ ተብለው የሚታመሱበት ጉዳይ ፍጹም አግባብነት የለውም፡፡ እንደ ኢዜማ አረዳድ ይህ አካሄድ በየትኛውም መመዘኛ ሕጋዊ መሠረት የሌለው ሲሆን ከአዲስ አበባ ት/ት ቢሮም ሆነ ከሚመለከተው የመንግስት አካላት በጽሑፍ የሰፈረ መመሪያና ትዕዛዝ ወደ ት/ቤቶች መተላለፍ አለመተላለፉን ለአዲስ አበባ ሕዝብ በግልጽ እንዲያሳውቁ አበክረን እንጠይቃለን፡፡
የነገው አገር ተረካቢ ትውልድ በዘር ፖለቲካ ትርክት ተፅዕኖ ሥር ወድቆ ለኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እና ብሔራዊ መዝሙር መቆርቆሩን የሀገር ተስፋ መሆኑን ማሳያ ምልክት ነው። ታዳጊ ተማሪዎች የሀገር ትርጉም ገብቷቸው ለኢትዮጵያ ሲሟገቱላት፤ በዕድሜ ታላላቆቻቸው ደግሞ በሀገር ቋሚ ምልክቶች ላይ ሲቀልዱ መመልከት በእጅጉ ያሳፍራል።
መጪው ትውልድ ሀገሩን የበለጠ እንዲወድ ማድረግ በሚገባቸው ትምህርት ቤቶች ከፋፋይ ትርክቶችን ማስተጋባት በሀገር ዕጣ ፈንታ ላይ መቀለድ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ለትምህርት ከቤታቸው የወጡ ተማሪዎችን ለግጭት መጋበዝም ኢ-ሞራላዊነት መሆኑም አፅንዖት ሊሰጠው ይገባል። በዚህ አጋጣሚም ተማሪዎች ለግጭት የሚጋብዟቸውን ድርጊቶች በትዕግስት፣ በሰላማዊ እና ስርዓት ባለው መንገድ በማስተናገድ ራሳቸውን ከጉዳት እንዲጠብቁ መልዕክት ማስተላለፍ እንወዳለን።
የፀጥታ አካላትም ተማሪዎችን ከጉዳት መጠበቅ እንጂ የሀይል አካሄድን በፍጹም መጠቀም እንደማይገባቸው እያሳሰብን የስርዓት ሳይሆን የህዝብ ጠባቂ መሆናቸውንም ለአፍታም ቢሆን እንዳይዘነጉት መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።
ምንም እንኳን መንግስታት በተቀያየሩ ቁጥር በሰንደቅ አላማችን መደብ ላይ በሚያርፈው አርማ ሙሉ ለሙሉ መግባባት ላይ ባይደረስም፤ ሕጋዊ ዕውቅና ያለውን የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ እና ብሔራዊ መዝሙር ማጉደፍ ግን በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሰሞኑን በአዲስ አበባ ት/ቤቶች በተነሱ ግጭቶች የተነሳ ጉዳት ለደረሰባቸው ተማሪዎችም ሆኑ ወላጆች የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ፤ ለእስር የተዳረጉት ተማሪዎች እና መምህራን በአስቸኳይ እንዲፈቱ ይጠይቃል።
ይህ ጉዳይ የሚመለከታቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ሆነ የፌደራል መንግስቱ ኃላፊዎች በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የሕዝብ ተመራጮች ለመረጣቸው ህዝብ ድምፅ ሆነው አስፈላጊውን ማስተካከያ እንዲደረግ ጫና ካልፈጠሩ እና ሁኔታውን የማያረጋጉ ከሆነ፣ ሂደቱ ወደ አላስፈላጊ ብጥብጥና አለመረጋጋት ከተሸጋገሩ የመጀመሪያ ተጠያቂዎች መሆናቸውን አበክረው ሊገነዘቡ ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
ህዳር 29/2015 ዓ.ም