የገዳ ባህል ካሪኩለም ተቀርጾለት በትምህርት መልክ በclass room ይሰጥ ከተባለ ሌሎቹ 85 ብሄር ብሄረስቦችም የራሳቸው ባህልና ትውፊት እንዲታወቅ ይጠይቃሉ::
ስለ ገዳም ስርአት ይሁን ስለ ሌሎች ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች እንደ ማህበራዊ ሳይንስ ባሉ የትምህትር ክፍሎች ማስተማር ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም። ሆኖም ሰሞኑን ጥያቄ የጫረው ጉዳይ የገዳ ስርአት እራሱን የቻለ የትምህርት ዘርፍ ሆኖ በአዲስ አበባ በመንግስት ትምህርት ቤቶች ሊሰጥ ነው መባሉ ነው።
አንዳንዶች እንደ መከራከሪያ የሚያቀርቡት የገዳ ስርአት እንኳን በኢትዮጵያ በውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ሳይቀር በPhD ደረጃ ይጠናል የሚል ነው። ትክክል ነው። ይሁንና በPhD ደረጃ የማይጠና ነገር የለም። በተለይ እንደ ሶሻል አንትሮፖሎጁ ባሉ የትምህርት ዘርፎች ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ጥልቅ ምርምርና ጥናት ይደረግባቸዋል።
ከተሳሳትኩ እታረማለሁ። እንደ እኔ ግንዛቤ አንደኛ የገዳ ስርአት በኦሮሞ ማህበረሰብ በሙሉ ተቀባይነት ያለው ወጥ የሆነ ስርአት አይደለም። ሁለተኛ የገዳ ስርአቱ አምልኮዊና ሃይማኖታዊ መሰረት ያለው ነው። በመሆኑም ከእምነቱ ነጥሎ ብቻውን “ዲሞክራሲያዊ ስርአት” ብሎ ማስተማር አሳሳችና ያልተሟላ ያደርገዋል።
ሶስተኛ መንግስት ፖለቲካዊ ውሳኔ ወስኖ በጀት መድቦ ሃይማኖታዊና አምሉኳዊ ትምህርት ለማስተማር መነሳቱ በተለይም በአሁኑ ጊዜ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። መንግስት በሃይማኖትና በአምልኮ ጉዳዮች ጣልቃ መግባት እንደማይገባው በህግ የተደነገገ ጉዳይ ነው።
የጋራ እሴታችን የሆነው ኢትዮጵያዊነት በኦሮሞ ህዝብ ስም በሚምሉና በሚገዘቱ ጽንፈኞች እየተውገዘና እየተጠቃ ያለበት ጊዜ ላይ መገኘታችን የማይካድ ሃቅ ነው። ዜጎች በማንነታቸውና በሃይማኖታቸው ምክንያት ብቻ እየተፈረጁ በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ፣ ቤት ንብረታቸው ሲቃጠል፣ ሲፈናቀሉና በሃገራቸው ላይ ከእነ ልጆቻቸው ስደተኛ ሲሆኑ ከዛም አልፎ ብዙ ጸያፍ የወገዛ ቃላት በየአደባባዩ ሲሰነዘሩ ድርጊቱን ያወገዘና አጥፊዎችን የገሰጸ አባ ገዳም አላየንም።
አምልኳዊ መሰረት ካለው ከገዳ ስርአት ይልቅ አፋን ኦሮሞና ሌሎችም ኢትዮጵያዊ ቋንቋዎች በየትምህርት ቤቱ ቢሰጡ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው የሚል እምነት አለኝ። ቋንቋ ሁሉ የመግባቢያ መሳሪያ ነው። ቋንቋ ማግባባት ብቻ ሳይሆን የበለጠ ልብ ለልብ ያቀራርባል፣ ባህላዊ እሴቶችንም ለመረዳት ያስችላል፣ መተማመንን ያዳብራል።
-Abebe Gellaw