በባህር ዳር የጅምላ ግድያ ተፈጽሟል። እየተፈጸመም ነው።
አገዛዙ ባለፉት ሶስት ቀናት በወሰደው እርምጃ ከ2ሺህ በላይ ሰላማዊ ዜጎች ተጨፍጭፈዋል። አሁንም የቀጠለ በመሆኑ ቁጥሩ ሊጨምር ይችላል። ከአንድ ቤት አምስት የአንድ ቤተሰብ አባላት ተገድለዋል። የአራት አመት ህጻን ልጅ ትገኝበታለች። ይህ የጦር ወንጀል ነው። አገዛዙ ንጹሃንን እየጨፈጨፈ ከተሞችን በማስጨነቅ ለመቆጣጠር መጠነ ሰፊ ዘመቻ ከፍቷል። በጎንደርም ቤት ለቤት ግድያ ተጀምሯል። ምህረት የለም። ህጻናትና አዛውንቶች እየተጨፈጨፉ ነው። በሸዋ ሮቢት ይኸው እርምጃ መወሰድ ከተጀመረ ቆይቷል። የአገዛዙ ኮማንድ ፖስት ይመጣና ”ጽንፈኞችን ደምስሼ ከተሞቹን አጽድቼአለሁ” የሚል መግለጪያ ይሰጣል። ኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ማጥፋት በሉት የጅምላ ፍጀት በአሁኑ ሰዓት እየተፈጸመ ነው።
ይሄን እንደ ወታደራዊ ድል ቆጥሮ አገዛዙ ደጋፊዎቹን እያስፈነጠዛቸው ነው። ባለኝ መረጃ ከፋኖ ህዝባዊ ሃይል አባላት በእነዚህ ጦርነቶች የተገደሉት ከ30 አይበልጡም። በአገዛዙ ቁጥጥር ስር የሚገኝ የፋኖ አባል ካለ እስከአሁን አልሰማሁም። በቃ! ድል የተባለው የንጹሃን እልቂት ነው። በድንጋጤ የሰነበተውን የአገዛዙን መንደር ለማረጋጋት በሚል በንጹሃን ፍጅትና እልቂት ከተሞቹን መልሶ መቆጣጠር እንደ መፍትሄ ተወስዶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው። ሃላፊነት የማይሰማው ጨካኝ አገዛዝ ማድረግ የሚችለውን አድርጓል። የህዝቡ ሰላምና ደህንነት የሚያስጨንቀው የፋኖ ሃይል ስልታዊ በሆነ መልኩ ከከተሞቹ ወጥቷል። የበለጠ እልቂት እንዳይፈጸም በሚል ያደረገውን ይህን የስትራቴጂ ለውጥ ከሽንፈት የቆጠረው አገዛዙ ከበሮ እየደለቀ ይገኛል።
የቀናት ጉዳይ ነገሮችን እንደሚለውጥ እርግጠኛ ነኝ። ቀድሞውኑ የትግሉ አላማ ከተሞችን ይዞ መቆየትም አልነበረም። ጨካኙ አገዛዝ ድሮን ጭምር በመታጠቅ፡ በየድንበሩ የሰፈረውን ሰራዊት ነቅሎ በማምጣት ህዝብ ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ ሲያውጅ ፋኖዎች ማድረግ የነበረባቸው ዞር ማለትን ነበር። አደረጉት። ይህ የጦርነት ባህሪ ነው። ለማንኛውም የባህርዳሩ ጭፍጨፋ እየተሰነደ ነው። የሚመክለከታቸው አካላት ማስረጃውን አጠናቅረው በዓለም ዓቀፍ የጦር ወንጀሎች ፍርድ ቤት እንዲታይ ማድረጋቸው አይቀርም። በግንባር ስላለው ሁኔታ ቀናትን መጠበቅ ነው። የሚሆነውን አብረን የምናየው ይሆናል።