ማፈሪያ አየር መንገድ… 😡
ስለ አቡነ ጴጥሮስ እንግልት መጋቢ ስርዓት ቀሲስ ጌታቸው በኒዋርክና አካባቢው ሃገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና ልዩ ፀሐፊ የተናገሩት ፦
<<ብፁዕነታቸው የጥምቀት በዓልን ለማክበር ወደ አሜሪካው ሀገረስብከታቸው ሐዋርያዊ ጉዞ ለማድረግ የተነሱት ከሶስት ሳምንታት በፊት ነበር።
እግረመንገዳቸውንም ብዙ የደከሙበትንና ስለእርቅ፣ ስለ ሰላምና ስለፍቅር የሚሰብከውን “የአቤል ደም” የተሰኘ መፅሐፋቸውን 500 ፍሬ ይዘው ለመሄድ ከሲኖዶስ አስፈቅደው ፣ ከቤተክነት ደብዳቤ ካስፃፉ በኋላ ለሐሙስ ጉዞ ዕሮብ ዕለት ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ጉምሩክ ሄደው ደብዳቤውን እና መፅሐፍቱን እንዲሁም ለካርጎ አገልግሎት የተጠየቁትን 103 ሺህ ብር ከፍለው ተመለሱ።
በማግስቱ ሐሙስ የበረራ ሰዓታቸው ተቃርቦ ወደ እቃ ፍተሻው ጋር ሲደርሱ ላፕቶፓቸውንና ስልካቸውን በኤርፖርቱ የፀጥታ አካላት ተቀሙ። ከቆይታ በኋላም ስልካቸውን በውስጡ ያለውን መረጃ ሁሉ አጥፍተው (Factory Reset) አድርገው ባዶውን ቀፎ መለሱላቸው።
ላፕቶፓቸውን ሲጠይቁ “ጭነነዋል ጭነነዋል ይሂዱ እዛው ይደርሶታል” ብለው ብጣሽ ወረቀት ሰጥተዋቸው ሄዱ።
Newark, New Jersey ሲደርሱ የተቀበልኳቸው እኔ ነበርኩ። ላፕቶፓቸውን ስንጠይቅ አልመጣም። ለምን? ብለን ስንጠይቅ “ከዛ አልተጫነም” ብለው መለሱልን። መፅሐፎቻቸውንም ብንጠብቅ ብንጠብቅ ማግኘት ስላልቻልን “በካርጎ በኩል ተረከቡ” ተባልን። እዛም ስንጠይቅ ከአዲስ አበባ እንዳልተጫነ ፈረንጁ የካርጎ ኃላፊ ኮምፒተሩ ላይ አሳየን።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ 103ሺ ብር ያስከፈለበት 500 መፅሐፍት የት እንዳደረሰው በማይታወቅ ሁኔታ ሳያስረክባቸው ቀረ።
ላፕቶፓቸው ደግሞ በዙሪያችን ባሉ ከአየርመንገዱ ጋር ግንኙነት ባላቸው ሰዎች ጥረት ከሳምንት በኋላ መጣ። እሱም ግን ልክ እንደ ስልካቸው ሁሉ መረጃው በሙሉ ከውስጡ ተጠረጎ ባዶ ቀፎው ነበር የመጣው።
ብፁዕነታቸው የመጡበትን አላማ ጨርሰው መመለሻቸው ሲደርስ ሰኞ ዕለት ከ John F Kennedy (JFK) ኤርፖርት ተነስተው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙበት ቀድሞ የተመዘገበ በረራቸውን ለማረጋገጥ ወደ አየር መንገዱ ሲደውሉ ስማቸው ከበረራው ላይ ተሰርዟል። “በኛ አየር መንገድ በረራ የሎትም” የሚለው ምላሻቸው ከመንግስት የበላይ አካል መመሪያ እንደተሰጣቸው ተረዳን።
የኒዋርክ ሀገረስብከትም የብፁዕነታቸው ሃሳብ ምን እንደሆነ ጠይቆ “እሄዳለሁ ! አልቀርም!” በሚለው ቆራጥ መልሳቸው መሄድ እንደሚፈልጉ ከተረዳ በኋላ ወዲያውኑ በአንድ በጎአድራጊና የቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ አማካኝነት “ከሀገረ ስብከቱም ወጪ አይወጣም” ብሎ በውድ ዋጋ ትኬት ተቆርጦላቸው በኤመሬትስ አየር መንገድ እንዲሄዱ ተደረገ።
ሰኞ በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር 6፡45 (ምሳ ሰዓት ገደማ) ላይ አዲስ አበባ ደረሱ።
አየሩ ማረፉን አረጋግጬ ከ15 ደቂቃ በኋላ ስደውልላቸው ግን ስልካቸው ይጠራል አይነሳም። የገመትነው ነገር እየሆነ እንደሆነ ተረዳን።
“ስልኮትን ሊቀሙ ስለሚችሉ በሌላ ሰው ስልክም ቢሆን እንድንገናኝ አመቻቹ” ብለን ባሳሰብናቸው መሰረት በሌላ ተሳፋሪ በማላውቀው የኢትዮጵያ ስልክ ደውለው አናገሩኝ።
“ይዘውኛል ፤ ሊመልሱኝ እያዘጋጁኝ ነውና ከዚህ በላይ ማውራት አልችልም” ብለውኝ ከ10 ሰከንድ በኋላ ተቋረጠ።
ከ20 ወይም 30 ደቂቃ በኋላ ስልካቸውን ምንም ሳያደርጉት መለሱላቸው። ደውዬላቸውም ምን እንደገጠማቸውም በደንብ አስረዱኝ ፦
ፓስፖርታቸውን ተቀብለው አይተው እንደመለሱላቸው፣ የሎው ካርዳቸውን ግን ተቀብለው “መግባት አትችልም” እንዳሏቸው፣ ምክንያቱን ሲጠይቁ ደሞ “Expire አድርጓል” እንደተባሉ፣ እሳቸውም “አንበው አንበው እንጂ የሰጣችሁኝ እራሳችሁ ናችሁ፤ የተሰጠኝ ለ5 ዓመት ነው የሚለው፤ ገና 2 ዓመቱ ነው፤ 3 ዓመት ይቀረዋል” ብለው ደጋግመው ቢያስረዱትም የደህንነት ኃላፊው ግን “በቃ አትገባም ! አትገባም” የሚል ምላሽ ብቻ እንደሰጣቸውና የሎው ካርዱን ይዞት እንደሄደ ነገሩኝ።
ከዛም የኤምሬትሱ አውሮፕላን ተዘጋጅቶ እስከሚመለስ ለ2 ሰዓታት ገደማ አስቀመጧቸው። በዛ መሃል የደረሰባቸው አካላዊ ጉዳት ምናምን ግን የለም። እንዳውም ጥሩ በመምሰል ለማነጋገር ይሞክሩ ነበር። የደህንነት ኃላፊው “ምን ይመክሩናል?” እያለ ሶስት ግዜ በተደጋጋሚ ሲጠይቃቸው ሶስቴም “ሰው ሁኑ” ብለው መልሰውለታል። ምናልባትም ክፉ ነገር አናግሮ ያንን መጠቀሚያ ለማድረግ ይመስላል።
በዚህ ሁኔታ 2 ሰዓት ገደማ ከቆዩ በኋላ የመጡበት የኤምሬትስ አውሮፕላን ዝግጁ ስለሆነ የደህንነት ኃላፊው ትኬት አስይዞ ወደዛው በማስገባት ወደ ዱባይ መለሷቸው።
ዱባይ ከደረሱ በኋላ ደሞ ኤምሬትስ አየርመንገድ ፓስፓርታቸውን ይዞ “እዚ የመጡበትንም ወደ አሜሪካ የምመልስበትንም ሂሳብ ክፈሉ” ብሎ ፓስፓርታቸውን ያዘ።
እሳቸውም “እኔ አምጡኝ አላልኳችሁም፤ የላከኝ ያ መንግስት ነው፤ አውሮፕላን ውስጥም ያስገባኝ ያለፍቃዴ ነው፤ እናንተም ተቀብላችሁ አምጥታችሁኛል፤ እንዳውም ወደ አሜሪካ የምሄድበትን ትኬት መስጠት ያለባችሁ እናንተ ናችሁ እንጂ እኔ ያንን ልከፍል አልችልም” አሉ።
እነሱም “ካልከፈልክ የትም አትሄድም” ብለው እንደ እስረኛ አደረጓቸው።
ከዛ በኋላ ነው በኛ በኩል ትኬታቸው ተስተካክሎ ወደዚህ እንዲመጡ ስራዎች መስራት የጀመርነው። ያለው ሁኔታ ይሄ ነው።>>
• የብሩክ ጥያቄ ፦
ቤተክርስትያኗ/ሲኖዶሱ ብፁዕነታቸውን ከቦሌ ኤርፖርት ለማስለቀቅ ለምን ፈጣን እርምጃ አልወሰዱም ? ወይስ አያውቁም ነበር ?
• የቀሲስ ጌታቸው መልስ፦
<<ቤተክርስቲያኗም ሆነ ሲኖዶሱ በደንብ ያውቃሉ። በምን አየርመንገድ እንደሚመጡና በስንት ሰዓት እንደሚገቡ ሁሉ አሳውቀናቸዋል። መረጃው አቡነአብረሃምም ጋ ደርሶ ከሌሎች አባቶች ጋ ሆነው ሊቀበሏቸው ቦሌ ኤርፖርት ተገኝተውም ነበር። ከአቡነ ጴጥሮስ ጋርም ፊትለፊት ተያይተዋል። እያዩዋቸው ነው መልሰው ወደ አውሮፕላን የወሰዷቸው። እንዲቀራረቡና ሰላምታ እንኳን እንዲለዋወጡ አልተፈቀደም።
አባቶቹ ከኤርፖርት ተመልሰው ስብሰባ ማድረጋቸውን ሰምተናል። አንዳንድ በዜና የወጡ ነገሮችንም አይተናል። ቤተክርስቲያኗን ይመጥናል አይመጥንም የሚለው አከራካሪ ቢሆንም>>
ብለዋል።
ጥንቅር፦ ፍፁም ምትኬ
ምንጭ፦ ኢትዮ 360
ሙሉ ንግግራቸውን ለመስማት ⬇