አገር ትልቅ አደጋ ተጋርጦባታል፡፡ መጋረጥ ብቻ አይደለም አደጋ ውስጥ ወድቃለች፡፡
1) በዜጎቿ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች እየተፈጸሙ ነው፡፡ ኢትዮጵያዉያን በተለይም አማርኛ ተናጋሪዎች በማንነታቸው በግፍና በጭካኔ እየታረዱ ነው፡፡ መንግስት አለ ይባላል፣ ግ ን መንግስት ብዙም የዜጎች ደህንነት ያስጨነቀው አይመስልም፡፡
ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ ከ300 ዜጎች በመተከል ሲታረዱ የአገር መሪ ነኝ የሚሉት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ፓርክና ሽርሽር ነው የሚያወሩት፡፡ በፌስ ቡክ ገጻቸውም የሚጽፉት፡፡
የዶር አብይ መስተዳደር የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ አልቻለም፡፡ ወይም አልፈለገም፤ ሆን ተብሎ በተለይም አማርኛ ተናጋሪዎች ከመተከል እንዲጸዱ ከመፈለግ የተነሳ፤ ወይም አቅምና ብቃት ስለሌለ፡፡
2) ሱዳን በመንግስት ደረጃ በይፋ የኢትዮጵያን መሬት ወራ ይዛለች፡፡ መውረር ብቻ አይደለም የበለጠም ለመዉረር እየዛተች ነው፡፡ በአጭሩ አነጋገር የኢትዮጵያ ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ተደፍሯል፡፡
የዶር አብይ መንግስት ጉዳዩን ከመደበስና ከመርመጥመጥ ውጭ ምንም ያደረገው ነገር የለም፡፡ እንደውም በጎንደር አካባቢ ያሉ ገበሬዎች ራሳቸውን እንዳይመከቱ በዲፕሎማሲ ስለምንፈታው አርፋችሁ ተቀመጡ ነው ያሏቸው፡፡
3) የዶር አብይ መስተዳደር ሰላማዊ የፖለቲካ መሪዎችን በግፍና በጭካኔ በማሰርና በማንገላታት፣ በአዲስ አበባ ዘረኛ የሆነ የተረኝነት አሰራርን በመዘርጋት፣ ታሪካዊ ቅርሶች በማፍረስ፣ ከሕዝብ ጋር እየተላተመ የመጣ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሕዝብ ድጋፍ እየተለየው ያለ፣ የህዝብ ድጋፍ መለየት ብቻ አይደለም በጣም እየተጠላ የመጣ መስተዳደር እየሆነ ነው፡፡
በኔ እይታ አሁን ባለው ሁኔታ በዶር አብይ አህመድ የሚመራው በፌዴራል መንግስት እንኳን አገርን ከአደጋ ሊያድን እንደውም የበለጠ የአገር አደጋ እንዲባባስ ምክንያትም እየሆነ ነው፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ የአመራር ለውጥና ሽግሽግ ካልተደረገ፣ ወሳኝና ድፍረት ያለው ውሳኔዎች መወሰን ካልተቻለ፣ በተለይም ትልቅ የአገር ነቀርሳ የሆነው ዳግማዊ ሕወሃት የኦሮሞ ብልጽግና አደብ እንዲገዛ ካልተደረገና ፣ በፌዴራል ደረጃ ከያዘው ተጽኖ ፈጣሪነት ቦታ ካልተነሳ፣ የበለጠ ትልቅ ችግር መፈጠሩ አይቀርም፡፡
ሶስት መፍቴዎች አስቀምጣለሁ፡
አንደኛ ፡ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊሶችና ሚሊሺያዎች ወደ መተከል በመንቀሳቀስ አካባቢውን ማረጋጋት እንዲጀመሩ መደረግ አለበት፡፡ ይሄንንም ለማድረግ የፌዴራል መንግስት ፍቃድ መጥበቅ የለባቸው፡፡ የዘር ማጥፋት ሲፈጸም ፍቃድ አልተሰጠኝም ብሎ ቁጭ ማለት በአለም አቀፍ Hግ መሰረት ራሱ ወንጀል ነው፡፡ መተከል ከነርሱ አቃም በላይ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ አካባቢዉን ያውቁታል፡፡ በመሆኑም በቶሎ፣ ብዙ ዜጎች እንደገና እየተደጋገመ ሳይታረዱ መግባት አለባቸው፡፡
ሁለተኛ ፡ የፌዴራል መንግስቱ ትኩረቱን ሱዳን ጋር አድርጎ መከላከያን ወደዚያ ማሰማራት አለበት፡፡ ነገሮችን መደባበቅ፣ አገር አስወርሮ መሽኮርመም መቆም አለበት፡፡ ያለውን ሁኔታ በግልጽ ለአለም አቀፍ ማህበረሰባትና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተገልጾ፣ ሱዳን በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለቃ የማትወጣ ከሆነ እርምጃ እንደሚወሰድ ማሳወቅ አለባት፡፡
እርምጃዉም በጎንደር በኩል ብቻ አይደለም፣ በሁሉም አቃጣጫዎች ሱዳን ላይ ወታደራዊ እርምጃዎች መወሰድ አስፈላጊ ነው፡፡
ኤርትራ የግብጽንና የሱዳንን አምሳደሮች ማበረሯ ተዘግቧል፡፡ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ የፈጸሙት ጥፋት አለ፡፡ ሆኖም በዋናነት እነርሱ ወደ ትግራይ እንዲገባ የፈቀደው አካል ነው መጠየቅ ያለበት፡ በመሆኑ ይህ ጉዳይ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ማድረጉ ላይ ግፊት አድርጎ ሊሰራበት ይገባል፡፡
ሆኖም ግን በዚህ ችግር ምክንያት በ ኤርትራን በኢትዮጵያ መካከል ያለው መቀራረብ እንዲደፈርስ ማድረግ አያስፈልግም፡፡ በዚህ ወቅት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጎን መቆሟ ትልቅ ነገር ነው፡፡
በመሆኑም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ባላት ትብብር፣ ከኢትዮጵያ ጋር በጦርነቱ ከተሳተፈች፣ በሰዓታት ከሰላን መቆጣጠር ይቻላል፡፡ከሰላ ብቻ አይደለም ጦርነት ቢጀመር በሰዓታት ውስጥ ሌላዋ ትልቋ የሱዳን ከተማ ገዳሪፍ መግባት ይቻላል፡፡ በመተከል በኩል ከቪክቶሪያ ሃይቅ የሚመጣው የናይል ወዝንና የአባይ ወንዝ የሚገናኙበት አካባቢ፣ በሱዳን የብሉ ናይል ክፍለ ሃገር ትልቅ ሃይቅ አለ፡፡ እዚያ ሃይቅ ዙሪያ ከ10 በላይ ከተሞች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ጦር በቀላሉ እነዚህን ከተሞች ሁሉ መቆጣጠር ይችላል፡ ያ ብቻ መሰላችሁ በቀላሉ ካርቱም መግባትም ይቻላል፡፡ በካርቱምና በመተማ መካከል እንዳለ ሜዳ ነው፡፡
በምእራብ በዳርፉር፣ በምስራቅ በቤጃዎች አካባቢ ሱዳን የራሷ አማጻያን ችግርም እየፈጠሩባት ነው፡፡ በርካታ ትልቅ የፖለቲካ ቀውስና ትርምስ አለባት፡
ምን አለፋችሁ፣ ጦርነቱ ከተጀመረ ሱዳን በቀላሉ እንደምትሸነፍ የሚያጠራጠር ነገር የለውም፡፡ ያ ብቻ አይደለም፡፡ ሱዳን እንደ አገርም ልትፈርስ ትችላለች፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥ ፣ ምን አልባትም የሱዳን ሕዝብ ራሱ በመሪዎቹ ላይ እንዲነሳ ሊያደርግም ይችላል፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ ግን ድካምንና ሽንፈትን ማንጸባረቅ አስፈላጊ አይደለም፡፡
ሶስተኛ ፡ የብልጽግና የስራ አስፈጻሚ እንደ ብልጽግና ነገሮችን መስመር ማስያዝ መቻል አለበት፡፡ ዶር አብይን ማንሳት አለበት፡፡ ያንን ማድረግ ካልቻለ፣ ምን አልባት በድርጅቱ ውስጥ አለመስማማቶች ከረው ከወጡ፣ ከብልጽግና ከመከላከያ ጀነራሎች፣ ከተወሰኑ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የተወጣጣ ከሱዳን ጋር እንዲሁም በመተከል ፣ በወለጋ ያሉ ችግሮች እስኪፈቱ ድረስ አንድ የአገር አድን የሽግግር መንግስት ቢመሰረት ጥሩ ነው፡፡